ኤች አይ ቪ ቫይረስን ለመከላከልና መቆጣጠር ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቆመ

ኤች አይ ቪ በሽታን የመከላከልና መቆጣጠር ሥራውን ለማጠናከር ሁሉም የባለድርሻ አካላት ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡  

የመቐለ ከተማ ነዋሪ ፍሬወይኒ መሃሪ በ1994 ዓ.ም በጋጠማት ድንገተኛ ህመም ፈውስን ፈልጋ ምርመራ ባደረገችበት ወቅት ቫይረሱ በደሟ እንደተገኘ ተናግራለች ።

 ፍሬወይኒ በወቅቱ የተፈጠረባትን መደናገጥና ተስፋ መቁረጥ በማሸነፍ ‘‘ወለዶ መድሃን ትግራይ’’ የሚሰኘውን ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝ ወገኖች ማህበር መቀላቀሏን ገልጻለች፡፡

በማህበሩ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ትውልድ ይዳን በኛ ይብቃ ብላ በማስተማር ወገንን በመታደግ ሥራ ላይ ተሰማርታ መቆየቷንና ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በመቐለ ሆስፒታል የፀረ-ኤች አይ ቪ ህክምና ክፍል በኬዝ ማናጀርነት እያገለገለች እንደምትገኝ ገልጻለች፡፡

ኤች አይ ቪ ኤድስ መከሰቱ እንደታወቀ የቫይረሱን ሥርጭት የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው የተጠናከረ እና አበረታች ውጤትም የታየበት እንደነበረ የምታስታውሰው ፍሬወይኒ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረውን ሃገራዊ ዝምታና መቀዛቀዝ ተከትሎ ሥርጭቱን የመከላከል ሥራው ተፈላጊውን ውጤት እያመጣ ባለመሆኑ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ትላለች፡፡

የኤች አይ ቪ ኤድስን በሽታ የመከላከልና መቆጣጠር ሥራው እንደቀድሞው ተጠናክሮ ካልቀጠለ የቫይረሱ ሥርጭት ሊያንሰራራ የሚችልበት እድል ሰፊ በመሆኑ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በሽታው እንዳይሰፋፋ ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉ ቫይረሱ በደማቸው የሚገኝባቸው ወገኖች አሳስበዋል፡፡  

በበሽታ ዙሪያ የተፈጠረው ዝምታና መዘናጋት ሊሰበርና የመከላከልና የመቆጣጠር ስራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉም አመልክተዋል፡፡