ባለሥልጣኑ በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በከተማይቱ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቅረፍ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከእነዚህ ሥራዎች መካከልም የትራፊክ መጨናነቅ እያስከተሉ ያሉ አደባባዮችን በማፍረስ በትራፊክ መብራት የመቀየር ሥራው መዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሠረት ከህዳር አንድ ከምሽቱ ሁለት ሰአት ጀምሮ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ እየፈጠረ ያለውን የቶታል ሶስት ቁጥር ማዞሪያ አደባባይ በማፍረስ በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ ስለሚያከናውን አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቋል፡፡  

ከጦር ኃይሎች የሚመጡ ተሸከርካሪዎች የቀራኒዮ እና ቤቴል በኩል ፤ ከብስራተ ገብርኤል የሚመጡ ተሸከርካሪዎች በመካኒሳ ቆሬ አደባባይ እና በመካኒሳ ሚካኤል ቤተክርስትያን በኩል እንዲሁም ከዘነብ ወርቅ በኩል የሚመጡ ተሸከርካሪዎች ደግሞ የአውጉስታ ቤቴል እና ቀራኒዮ ተለዋጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባደረሰን መረጃ አስታውቋል፡፡