የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በፎረንስክ ምርመራ በጋራ ለመስራት ተስማሙ

የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒዬም ሜዲካል ኮሌጅ ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመሆን በፎረንስክ ምርመራ ሥራ ላይ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡

የሆስፒታሉ ብሔራዊ የፎረንስክ ማዕከል ከዚህ ቀደም ማንኛውንም የህክምናና የህግ ጉዳዮችን እንደሚያስተናግድ ይታወቃል ።

ሆስፒታሉ በአስገድዶ መድፈር፣ የዕድሜ ምርመራ፣ በመኪና ጉዳት የደረሰባቸው የአካል ጉዳቱን መግለጽ እና ሌሎችንም ከህግና ከፍትህ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን በህክምና ሙያዊ በሆነ መልኩ ባለሙያዎችን ለማሠልጠን እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል፡፡

ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በተፈራረመው ስምምነትም ለፖሊስና ህግ ባለሙያዎች የፎረንስክ ሜድስንና የፎረንስክ ሳይንስ ከተግባራዊ ዕውቀት ጋር ወንጀልን መመርመርና ለፍርድ ቤት ሪፖርት ማቅረብን በተመለከተ ሆስፒታሉ ሥልጠና እንደሚሠጥም ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ውስጥ ብሔራዊ የፎረንስክ ሜድስንና የፎረንስክ ሳይንስ ተቋማትን ለመመስረት ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በጋራ እንደሚሰራ አስታውቋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተካሄደው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ለአምስት አመታት እንደሚቆይም ተገልጿል፡፡