የኤች አይ ቪ ኤድስን ሥርጭት ለመከላከል አስፈጻሚ አካላትና ህብረተሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

በአገሪቱ  በአሳሳቢ ደረጃ  ላይ  የሚገኘውን  የኤች አይቪ ኤድስን ሥርጭት  ለመከላከል  አስፈጻሚ አካላትና ህብረተሰቡ የድርሻቸውን እንዲወጡ የፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ጥሪ አቀረበ ።

የፌደራል ኤች አይቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጣሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ገብረመድህን በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን  እየተወጡ  ባለመሆኑ  ምክንያት የኤች አይ ቪ ኤድስ ሥርጭት አሳሳቢ  ደረጃ ደርሷል ብለዋል ።

ከዚህ ቀደም ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከል ከውጭ አካላት ሲመደብ የነበረውን በጀት  በከፍተኛ ደረጃ  መቀነሱና መቋረጡም  በሽታው  እንዲያንሠራራ ምቹ  ሁኔታን  መፍጠሩን  ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።

በከፍተኛና አገር አቀፍ የትራንስፖርት አገልግሎት የተሠማሩ ዜጎች፣ ሴተኛ አዳሪዎች፣ የትዳር የፈቱ ሰዎች የከፍተኛ  ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች  ለኤች አይቪ ኤድስ በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል እንደሚገኙበት በመግለጫው ተመልክቷል።     

ኤች አይ ቪ ኤድስ ማህበራት የሚያደርጉት እንቅስቃሴዎች መዳከምና እንዲሁም የህግ  አውጭና አስፈጻሚ አካላት ክትትል ማነስም ለበሽታው ሥርጭት መጨመር የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉን  ምክትል ዳይሬክተሩ አስረድተዋል ።

በኢትዮጵያ  እስከ 2012 ዓም ድረስ የሦስቱ 90ዎች ዕቅድን  መሠረት  በማድረግ ለኤች አይቪ ኤድስ  ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ  ክፍሎች  90 በመቶ የደም  ምርመራ  እንዲያደርጉ፣ አስፈላጊውን  ምርመራ  ካደረጉ በኋላም  የህክምና ክትትል በማድረግ  አስፈላጊውን መድሓኒት  እንዲወስዱ የሚያስችል መርሃ ግብር  እየተካሄደ  ይገኛል ።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ገለጻም በአገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው መርሃ ግብሩም እስካሁን 75 በመቶው እየተሳካ በመሆኑ በ2012 ዓም ሙሉ ለሙሉ ስኬታማ እንደሚሆን ተገልጿል ።

በተያያዘ ዜና የዘንድሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ ቀን  “ ለኤች አይ ቪ ይበልጥ  ተጋለጭ ነን  እንመርመር  እረሳችንን  እንወቅ ”   በሚል  መሪ ቃል የኢፌዴሪ  ፕሬዚዳንት ፣ ሚንስትሮችና የክልል ተወካዮች  በተገኙበት ህዳር 22 ቀን  በዱከም ከተማ  እንደሚከበር በመግለጫው ተመልክቷል ።

የኤች አይ ቪ ኤድስን ሥርጭት ለመግታትም የሚዲያ አካላት ከሚመለከታቸው  ባለድርሻዎችና ማህበራትና ህብረተሰቡ ጋር ርብርብ የሚያደርግ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ  ጠቁሟል ።

እኤአ በ2030 በመላው ዓለም ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመግታት ዕቅድ የተያዘ  ሲሆን ኢትዮጵያም  በዚህ ረገድ  የድርሻዋን ለመወጣት  እየሠራች እንደምትገኝም ተገልጿል  ።