የከተሞች ዕድገትን ከፈጣን የሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተመጣጣኝ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ

የከተሞች ዕድገት ፈጣን ከሆነው የህዝብ ቁጥር ዕድገት እና ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር የተመጣጠነ ለማድረግ  አስቀድሞ መሥራትን አስፈላጊ መሆኑ  ተጠቆመ፡፡

በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በተጀመረው 17ኛው አለም አቀፍ የከተሞች ጉባኤ ላይ  እንደተገለጸው በዓለም የሚገኙ ከተሞችን ዕድገት ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር ተመጣጣኝ  ለማድረግ   ቀደም ብሎ አቅዶ  መሥራት  እንደሚያስፈልግ  ተገልጿል ።

በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 20 እና 21 ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 17ኛው ዓለም አቀፍ የከተሞች ኮንፈረስ ላይ የተለያዩ የባለድርሻ አካላት  ታዳሚ መሆን ችለዋል  ፡፡

 ጥሪ የተደረገላቸው የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች፣ የአውሮፓ ሀገራት ልዑካንና ተወካዮች በመርሃ-ግብሩ ተሳታፊ የሆኑ ሲሆን በከተሞች እድገት ዙሪያም ውይይት አድርገዋል፡፡

የከተሞች የወደፊት እድገትን መሠረት አድርጎ እየተካሂደ በሚገኝው በዚህ ጉባኤ ላይ የከተሞችን እድገትና ተያይዘው የሚመጡ ተጓዳኝ ጎዳዮች ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

በቀረቡ በጥናቶቹ መሰረትም በአለም ከሚገኙ ህዝቦች ውስጥ 2ነጥብ 5 ቢሊየን ያህሉ ኑሮውን በከተማ ውስጥ  ማድረጉ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ውስጥ ደግሞ በአፍሪካና በእስያ አህጉራት የሚገኙ ከተሞች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡

40 በመቶ የሚሆነው ወይንም 500 ሚሊዮን ያህሉ የአፍሪካ ህዝብ  ኑሮአቸውን የመሠረቱ በከተማ ውስጥ መሆኑ  ተገልጿል ፡፡

በሚቀጥሉት 10 አመታት  1.4 ቢሊየን የሚሆኑ አፍሪካውያን ኑሯቸውን በከተማ ውስጥ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ሲል የቀረበው ጥናት ቅድመ-ግምቱን አስቀምጧል፡፡

 በመሆኑም ከከተሞች እድገት ጋር ተያይዞ በከተሞች የሚፈጠረውን የህዝብ ቁጥር ብዛት እና ገቢን በማመጣጠን የሰዎችን ኢኮኖሚ ማሳደግ ብሎም ሥራ አጥነትን መቀነስና የትራንስፖርት ችግርን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ሥራ መሥራት እንደሚገባ በጥናቱ ተነስቷል፡፡

ኢትዮጵያም ይህንኑን ልምድ በመቅሰም የተቀናጀ የከተማ እድገትን ለመከተል የተለያዩ ስራዎች እንደሚሰሩ የአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር ተወካይ አብራርተዋል፡፡

በጉባኤው ላይ  የከተሞችን ፈጣን እድገት ተከትሎ በከተሞች የህዝብ ቁጥር መጨመር አንዱ ፈተና መሆኑና በአፍሪካ ከሚገኙ ህዝብ ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው እድሜያቸው ከ15-35 ወጣቶች መሆናቸው ተመልክቷል ።

በአጠቃላይም የከተሞች እድገት ወጣቱን ያማከለና ተጠቃሚነቱንም ሊያረጋግጥባቸው  የሚችሉ  መሆን እንዳለባቸውም  በጉባኤው  ላይ ተጠቅሷል ፡፡