በአዲስ አበባ ዙሪያ የልማት ተነሺ ዜጎች ተገቢው ካሳ ያልተሠጣቸው በመሆኑ ለችግር መዳረጋቸውን ገለጹ

በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙና ካለፉት አምስት ዓመታት ጀምሮ በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ  ዜጎች  ተገቢው ካሳ ስላልተሠጣቸው ለችግር መዳረጋቸውን ገለጹ ።

ዋልታ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ በልማት ምክንያት ከይዞታቸው የተነሱ ዜጎች እንደገለጹት መንግሥት ከይዞታቸው ሲነሱ በካሬ ሜትር አነስተኛ የካሳ ገንዘብ የሠጣቸው በመሆኑ  አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል ።

በአዲስ አበባና  ዙሪያ  በልማት  የተነሱት  ዜጎቹ ከ 2005 ዓም  ጀምሮ ለእርሻ መሬታቸው  18 ብር ፣ለግጦሽ መሬት ደግሞ  በካሬ ሜትር 11 ብር  ተሰልቶ የተሠጣቸው በመሆኑ ኑሯቸውን  ለመምራት  አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሮባቸው እንደቆየ አስተያየታቸውን ገልጸዋል ።                

የልማት ተነሺዎቹ መንግስት የካሳ ሁኔታውን መልሶ በማየትም ይህን ጉዳይ ፈትሾ መፍትሄ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል ።                     

የአዲስ አበባ አስተዳር ከንቲባ ሰሞኑን ከልማት ተነሺዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም በተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች የሚገኙ የልማት ተነሺዎች ካሳን በተመለከተ ተመሳሳይ ቅሬታዎችንም  ማቅረባቸው ይታወሳል ።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ባደረጉት ግብዣም በትናንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ አካላት በተለይ በኩዩ ፈጬ የጋራ መኖሪያ ቦታ አካባቢ በመገኘት ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውን ዜጎች  ጎብኝተዋል  ።