በሰባት ከተሞች ከተሸከርካሪ ፍሰት የፀዱ የመንገዶች ቀን ተጀመረ

በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል ከተሞች ከተሸከርካሪ ፍሰት የፀዱ የመንገዶች ቀን ትናንት  ተጀምሯል ። 

ትናንት በአዲስ አበባ የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር  ዶክተር አሚር አማን በተገኙበት ነው  የክልል ከተሞች ከተሽከርካሪ  ፍሰት  የፀዳ የመንገዶች  ቀን በይፋ ተጀምሯል።

የጤና ጥበቃ  ሚኒስቴር  የከተማ መንገዶችን በተወሰነ መጠን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ በማድረግ የሚከናወን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችንና አጋላጭ መንስኤዎቻቸውን ለመከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል መርሃ ግብርን ይፋ አድርጓል ።

በዚህም መሰረት በወር አንድ ቀን ወሩ በገባ የመጨረሻውን እሁድ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተመረጡ መንገዶችን ከተሽከርካሪ ፍሰት ነፃ የሚያደርግ መርሃ ግብር ነው ።

ከትራፊክ  ነጻ በሆኑ  መንገዶችም የተለያዩ ጤናን ለሚያበለፅጉ የአካል እንቅስቃሴዎች ለመስራት፣ ጤናማ የአኗኗር ዘዴ መልዕክቶችን ለማስተላለፍና ለተለያዩ የጤና ቅድመ ምርመራ ስራዎችን ለማከናወን ያስችላልም ተብሏል።

“ጤናማ የኗኗር ዘዴ ለጤናማ ህይዎት” በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ትናንት  በይፋ ሲጀመር የተለያዩ ታዋቂ ሰዎች ተገኝተዋል ።

በሰባት ከተሞች ላይ ከተሽከርካሪ ነፃ በሆኑ የተመረጡ መንገዶች መርሃ ግብር ሲጀመር የአካል እንቅስቃሴዎች፣ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች ነፃ ምርመራዎች እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተከናውነዋል።