ቤተክርስቲያኗ በአገሪቱ እየታዩ የመጡ ግጭቶችን ለማርገብ የአንድነትና የሰላም ስምሪት ልታካሄድ ነው

በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ የመጡትን ግጭቶች ለማርገብእና ሰላምን ለማስፈን  የሚያስችል  የአንድነት እንዲሁም  የሰላም ስምሪት ከታህሳስ 10 ቀን ጀምሮ በመላው አገሪቱና  በውጭ  አገራት  እንደሚካሄድ  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች ።

የመንበረ ፓትሪያሪክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አባ ዲዮስቆሮስ በዛሬው ዕለት  ለመገናኛ ብዙሃን በሠጡት መግለጫ የሰላምና የአንድነት ስምሪትም የሚያስተምሩና ሥልጠና የሚሠጡ የአባቶችና የካህናትና ሥልጠናም በይፋ መጀመሩን ገልጸዋል ።

በሰዎች መካከል ሰላምን የሚያሳጣ አንድነትን የሚያጠፋና ፍቅርን የሚንድ የህዝብን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል መጥፎ ትምህርትን በማሠራጨት  ሰውን በሰው ላይ ፣ ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሱትን ለመግታት  የሰላምና የአንድነት  ትምህርት እንደሚሠጥ የጠቅላይ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ አባ ዲዮስቆሮስ  በመግለጫቸው አስረድተዋል ፡፡

የሀሰት ትምህርቶችን በይፋ በመስበክ በአንድነት የኖረውን ህዝብ በመከፋፈል ህፃናትን እና ወጣቶችን ለጥፋት የሚዳርጉ ተግባሮች እየተበራከቱ በመምጣታቸው ቤተክርስቲያኗ  በመታዘቧ  ሰላምን እና አንድነትን የመስበክ ኃላፊነቷን ለመወጣት መንቀሳቀስ እንደምትጀምር ተመልክቷል ።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የምትታወቅበትን የሰላምና የመረጋጋት ተምሳሌታዊ ሀገር እንድትሆን የሚያስችል ተግባርን እንደሚከናወንም የጠቅላይ ፅህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ  ተናግረዋል፡፡

የተመረጡት የሰላም ልዕካኑም የሚጠበቅባቸውን መንፈሳዊና ማህበራዊ ብሎም ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ግዴታ እንዲወጡ  ኃላፊነት   የተጣለባቸው መሆኑን ጠቁመዋል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀገር ላይ መረጋጋት እንዲመታና ሰላም እንዲሰፍን ለማስቻል በመላ ሀገሪቱ እና በውጭ ሀገራትም ሰላም እና አንድነትን የሚሰብኩና የሚያሰተምሩ ከ150 በላይ የአባቶች እና የካህናት ሥልጠናም መሥጠት መጀመሩ ተገልጿል፡፡