አዲሱን የትምህርት ፍኖተ ካርታ በአግባቡ ለማስፋት የሚያስችል ጽህፈት ቤት ተቋቋመ

አዲሱን የትምህርት ፍኖተ  ካርታ  በአግባቡ  ለማስፋት  የሚያስችል  ጽህፈት ቤት  በትምህርት ሚኒስቴር  ሥር   መቋቋሙን  የትምህርት ሚኒስቴር  አስታወቀ ።

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ  በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት በአጠቃላይ  የትምህርት ፍኖተ ካርታ ሥራውን ለማሻሻል የሚያስችለውን መነሻ  ለጠቅላይ ሚንስትር  ጽህፈት ቤት እንዲቀርብ  ተደርጎ  ፀድቋል ።

በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም የባለድርሻ አካላት የተካተቱበት ውይይቶች  ተካሄደው የተጨመቀው  ሓሳብ  መዘጋጀቱንም  ሚኒስትሩ ዶክተር  ጥላዬ  ጌቴ በመግለጫው ተናግረዋል ።

ፍኖተ ካርታው በተመለከተ በተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር የውይይት መድረክም 700ሺህ ያህል ሰዎችም  ታሳታፊዎች  መሆናቸውም   ተገልጿል  ።

በፍኖተ ካርታው ውይይት ወቅት የአንድ ዜጋ የትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ 6 ወይም 7  እድሜ ይሁን በሚል የትኩረት ሓሳብ  ላይ ውይይት የተደረገ መሆኑ የገለጹት ዶክተር ጥላዬ ዩኒቨርስቲ  ለመግባት  የሚያስችለው ትምህርት እስከ 10ኛ ወይም 12ኛ ድረስ ይሠጥ የሚለው ሌላው  መከራከሪያ ነጥብ እንደነበር ገልጸዋል ።

በአገሪቱ ካለው የመጀመሪያ ደረጃ የትምህርት ተደራሽነት አንጻር የህጻናት ትምህርት መጀመሪያ ዕድሜ  7 ቢሆን  እንዲሁም ዩኒቨርስቲ ለመግባት  እስከ 12ኛ ክፍል  ድረስ ማጠናቀቅ   ጠቃሚ  እንሚሆንም  በትምህርት  ፍኖተ ካርታው በጉልህ  የተነሱ ሓሳቦች  መሆናቸውንም ዶክተር  ጥላዬ ገልጸዋል ።

የመማር ማስተማር ሂደቱን በተመለከተ ከውጭ የሚቀመሩ የትምህርት  ፖሊሲዎች እንዳሉ  የጠቀሱት ዶክተር ጥላዬ  አገር በቀል እውቀቶች  በስፋት  በመማር  ማስተማሩ ላይ  ተግባራዊ  እንዲደረጉ  በፍኖተ  ካርታ ውይይቱ  ተጠይቋል ።    

በተጨማሪም  ተማሪዎች  እስከ 12ኛ ክፍል  ከተማሩ  በኋላ  በዩኒቨርስቲ  በሚገቡበት  ወቅት  የመጀመሪያ ዓመትም የአገራቸውን  ታሪክ  እንዲማሩ  የሚደረግ መሆኑም በፍኖተ  ካርታው  መድረግ ላይ  የተነሳ ጉዳይ መሆኑ ተገልጿል ።

በአጠቃላይ  በአገሪቱ  በመጀመሪያ ደረጃ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ፣ ከፍተኛ  ሁለተኛ ደረጃና  ዩኒቨርስቲ  የሚያስተምሩ መምህራንም  ደረጃ  የሚያስቀምጥ   አዲስ  አሠራር በፍኖተ ካርታው ተግባራዊ  የሚደረግ  መሆኑንም  ሚኒስትሩ አብራርተዋል ።

እስካሁን  ድረስ በትምህርት ፍኖተ  ካርታው ላይ  በተደረገው  ውይይትም  የተለያዩ  የባለድርሻ አካላት ተሳታፊነት  የተካሄደ  መሆኑንና   መንግሥት  እስከ  አርብቶ አደርና አርሶአደሩ  ድረሰ የሚገኙ የህብረተሰብ  ክፍሎች  ሊወያዩበት  ይገባል የሚል አቋም  እንዳለውም  ሚኒስትሩ ገልጸዋል ።

በትምህርት  ፍኖተ ካርታ  ዙሪያ  በመላ አገሪቱ  ሁሉም  ወረዳዎችና ቀበሌዎች  በሚቀጥለው  ሳምንት በፍኖተ ካርታው  ላይ ውይይት እንዲያደርጉ  ዝግጅቶች  የተጠናቀቁ ሲሆን  ለዚሁም ተግባር  ከፌደራልና  ክልል  ተቋማት  ጋር ስምምነት ላይ መደረሱንም  ሚኒስትሩ አብራርተዋል ።

የትምህርት ፍኖተ ካርታው ስኬታማ እንዲሆን  የመገናኛ ብዙሃን  የበኩላቸውን  ሚና  እንዲወጡ የትምህርት  ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል ።