በታንዛኒያና ሊቢያ የሚገኙ 80 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው መመለሳቸው ተገለጸ

በታንዛኒያ እና ሊቢያ የሚገኙ 80 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቀ፡፡

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅና መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህይወታቸው ለአደጋ ተጋልጦ የነበሩ ዜጎችን ከታንዛንያ እና ሊቢያ መመለሱን አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት የታንዛንያ መንግስት  ህጋዊ የጉዞ ፈቃድ ሳይኖራቸው ወደ አገሩ የገቡ 231 ኢትዮጵያውያን ክሳቸው ተቋርጦ ምህረት እንዲያደርግላቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በመደረጉ ዛሬ ጠዋት 65 ወገኖቻችን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

ቀሪዎቹንም ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይ.ኦ.ኤም) ጋር በመተባበር እንዲመጡ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

ከስደት ተመላሹቹ መንግስት በችግር ላይ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ለሠጠው ድጋፍና እስከ አገር ቤት ለመመለስ ላደረገው ጥረት አመስግነው በአገራቸው ለመለወጥ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡  

በሌላ በኩል ካይሮ የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ ሊቢያ ከሚኖሩ ሌሎች በጎ አድራጊ ኢትዮጵያውያን እና የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (አይ.ኦ ኤም) ጋር በመተባበር 15 ወገኖቻችን ዛሬ ከትሪፖሊ ወደ አገራቸው መመለስ መቻሉንም አስታውቋል፡፡

የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትገኘው ሊቢያ ደህንነታቸው ለአደጋ ተጋልጦ የነበሩ 21 ወገኖቻችን ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ወደ አገራቸው መመለስ ተችሏል።

በተመሳሳይ ዜና ሱዳን የሚገኘው የኢፌዲሪ ኤምባሲ ከአገሪቱ ፖሊስ ጋር በመተባበር በህገወጥ አዘዋዋሪዎች ታግተው የነበሩ 15 ኢትዮጵያውያንን ከታሰሩበት አስፈትቷል።

አጋቾቹ ዜጎቻችንን ከካርቱም አቅራቢያ ሀጃር የተባለ ቦታ ለብዙ ሳምንታት በማገት እና ወደ ኢትዮጵያ በመደወል የታሳሪዎቹ ቤተሰቦችን ገንዘብ ካልተላከላቸው እንደሚጎዷቸው በስልክ ሲያስፈራሯቸው እንደነበርም ተገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 2250 ኢትዮጵያውያን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገራቸው መመለሱ ይታወቃል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)