ኢንስቲትዩቱ በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማእከል ለመሆን አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ በ13 የሥልጠና ዘርፎች አራት መሰረታዊ ግቦችን አንግቦ በውሃ እና ሳኒቴሽን ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ተግባር ተኮር ሥልጠና አየሰጠ እንደሚገኝ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ታመነ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ውሃን በቀላል ቴክኖጂዎችና በዝቅተኛ ወጪ ከመሬት ውስጥ በማውጣት በተለያዩ ክልል ባሉ ወረዳዎች የንጹህ መጠጥ ዉሃን ለማዳረስ ባለሙያዎችን እያሰለጠነ ነው ብለዋል፡፡

ተቋሙ ውሃን የጸሐይ ብርሃንን በመጠቀም በቀላሉ ከከርሰምድር በማውጣት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ማስቻሉን አቶ ታመነ ገልጸዋል፡፡

አሁን የሚሰጣቸውን ሥልጠናዎች ለማድረግ ወጪያቸው በኢትዮጵያና በሞሮኮ መንግስት የተሸፈኑ የውሃ ፍሳሽ ማጣሪያና የስፔሻላይዝድ ላብራቶሪ የሚያገለግሉ ህንጻዎችን እየገነባ ሲሆን ግንባታዎቹ ሲጠናቀቁ ተቋሙ የምስራቅ አፍሪካ የልህቀት ማዕከል የመሆን ዕቅዱን ያሳካል ሲሉ የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዋሲሁን አለማየሁ ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ የንጹህ መጠጥ ውሃንና ሳኒቴሽንን በጋራ አቀናጅቶ የሚሠራ ሲሆን ኢትዮጵያ የምትከተለውን ዋን ዋሽ ፕሮጀክት ለማሳካት ሳቶ የተሰኘ ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶች አሠራር ዙሪያ ሠርቶ ማሳያ ሥልጠና አካቶ እየሰራ እንደሚገኝ አቶ ዋሲሁን ተናግረዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡት የዲአይ ሥልጠና ተከታታይ የሆኑት አቶ ደመላሽ ሙሉ እና ለመሳ ወያ በኢንስቲትዩቱ የሚሠጣቸው ሥልጠናዎች ተግባር ተኮር በመሆናቸው ክህሎታቸውን ከማሳደግ ባሻገር በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመሥጠት እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ሥልጠና የሚሰጥባቸው መሳሪዎች ዘመናዊ ቢሆኑም አንዳንድ መሣሪዎች መሻሻል እንዳለባቸው ሠልጣኞቹ ጠቁመዋል፡፡