የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት ተካሄደበት

የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ በዛሬው ዕለት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

ጥናቱን ለምክር ቤቱ አባላት ያቀረቡት የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በሥራ ላይ ያለው የሥርዓተ ትምህርት በርካታ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ፍኖተ ካርታውን ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡  

የትምህርት ሥርዓቱ እየተፈተሸ የማይከለስና ሀገር በቀል እውቀቶች ያልተካተቱበት በመሆኑ ብቁ ዜጋ ማፍራት እንዳልተቻለ እና የተማሪዎች ምዘና ችግር እንደነበረበት ጠቁመዋል፡፡                         

በሌላ በኩል የመምህራን ብቃት አሁን ባለበት ሁኔታ አነስተኛ በመሆኑ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥራት አለመኖሩ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ችግር መሆኑን ዶክተር ጥላዬ ገልጸዋል፡፡

የፍኖተ ካርታው ፍልስፍናና ማሻሻያው የሀገሪቱን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን መሆኑን የጠቅሱት ሚኒስትሩ በሀገሪቱ ያለውን የትምህርት ስርዓት ላይ ያሉትን ችግሮችና የመፍትሔ አቅጣጫውን የለየ ነው ብለዋል፡፡

በቀረበው ጥናቱ ዙሪያ አስተያየት የሠጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ፣ ብቁ መምህራንን በማፍራት ረገድና ለሀገሪቱ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ዜጋ ከማፍራት አኳያ አዲሱ ማሻሻያ በሚያመጣው የመፍትሔ ሐሳቦች ዙሪያ ጥያቄዎችን አንስተው ትምህርት ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡