የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የክትትልና ቁጥጥር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የክትትልና ቁጥጥር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ምክክር ያደረገ ሲሆን በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር ሂደት ላይ የሚታዩ ችግሮችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት ተደርጓል።

በመድረኩ ላይ የትምህርት ጥራት ችግር፣ የመረጃ አያያዝ ችግር፣ደንብና መመሪያ ጠብቆ ያለመሥራት፣ ወጥነት ያለው የውጤት አሠጣጥ ያለመኖር እና ሌሎች ችግሮች በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ እንደሚስተዋልበት ተነስቷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ወልደማርያም የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዜጋን በመቅረጽና ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፍላጎት የሚሆን የተማረ ኃይል እንደሚያበረክቱ ገልጸው አሁን ላይ በግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በኩል የሚታዩ ችግሮችን መፍታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል።

ለዚህም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ለመደገፍ የክትትልና ቁጥጥር ማዕቀፍ መዘጋጀቱን የተናገሩት ሚኒስትሯ ከዚህ ባለፈ በሁለቱ አካላት መካከል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያግዝ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ማዘጋጀቱንና የመማክርት ጉባኤ መቋቋሙን ገልጸዋል።

ይህም ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ትኩረት በመሥጠትና አብሮ ለመሥራት የሚያስችል አሠራሮች እየተዘረጋ እንደሆነና ከዚህ ባለፈም በመንግስት በኩል ለግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ይደረጋልም ነው ያሉት።  

የተቋማትን ፍትሃዊ ተደራሽነትን ማሳደግ፣ ሥልጠናዎችን በመሥጠትና ልምድ ልውውጦችን በማድረግ የአመራሩንና ፈፃሚውን ብቃት ማሻሻል፣ ልዩ ልዩ ማዕቀፎችንና ደረጃዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ፣ የመረጃ አያያዝ ችግሮችን መቅረፍ፣ ከግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበራት ጋር በቅንጅት መሥራት እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥርዓትን ማጠናከር በቀጣይ ትኩረት የሚሰጥባቸው ሥራዎች እንደሆኑ በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል፡፡

የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከመንግስት በኩል የሚደረገው ድጋፍና ክትትል አናሳ መሆኑን አንስተው አሁን ተስፋ ሰጪና ጥሩ ጅምር እንዳለው ገልጸዋል፡፡