የወገኖቻችን ሞት ፣ መፈናቀልና ጉዳት በአፋጣኝ በማቆም ሁሉንም ወገን ቅድሚያ ለአገራዊ አንድነት፣ ሰብዓዊ ክብርና ሰላም ሊተጋ እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ ።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በዛሬው ዕለት በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት በአገሪቱ የሚታየውን አለመረጋጋትና ውጥረት በማርገብ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር በሚያስችለው “ ሰላም ለሁላችን ፣ በሁላችን!” በሚል መሪ ቃል የሚደረገው የሰላም ጉዞ መጀመሩን ገልጸዋል ።
በተጀመረው የሰላም ጉዞና ምክክር መድረኩ በተለያዩ ክልሎች የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት በወቅታዊ የአገሪቱ ሁኔታ ችግሮችና መፍትሔዎች ላይ ምክክር ማድረግ ተችላል ብሏል መግለጫው ።
ለዘመናት በመከባባር የኖሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖች በመካከላቸው አለመከባበርና አለመተማመን የሚፈጥሩ ተጨባጭ ችግሮችም እየታዩ መሆናቸውን መገንዘባቸውን ባወጡት መግለጫቸው አትተዋል ።
በአገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች በሚፈጠረው ግጭት በየዕለቱ የንጹሓን ዜጎች ደም በከንቱ እየፈሰሰ ፣ ወገኖችም እየተፈናቀሉና ለእንግልት እየተጋለጡም መሆኑን መግለጫው አብራርቷል ።
መግለጫው በተጨማሪም እየተስተዋሉ ያሉት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች መነሻቸው የትኛውም ይሁን ለአገር ሰላምና ወገን ደህንነት በማሰብ ችግሮችን በወይይት መፍታት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል ።
በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የበላይ አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በጋራ በመሆን ለመላው ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሰላም መልዕክትና ተማጽኖ የሚያስተላልፍ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ጥሪያቸውን አቅርበዋል ።