ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገኘውን የካንሰር ማዕከል ጎበኙ

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሚገኘው የካንሰር ማዕከል ተገኝተው ህክምናቸውን በመከታተል ላይ የሚገኙ ህጻናትና ልጆችን ጎበኝተዋል፡፡

ካንሰር በማህበረሰቡ ላይ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመከላከል መላው ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ እንዲጫወትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሚገኘው የካንሰር ማዕከል 42 የሚደርሱ አልጋዎች ብቻ ቢኖሩትም ተቀብሎ የሚያስተናግዳቸው ህጻናትና ልጆች ግን በየጊዜው ቁጥሩ በከፍተኛ መጠን እያደገ መምጣቱ ተገልጿል፡፡

ከአልጋ እጥረት በተጨማሪ የካንሰር መድኃኒት እጥረትም የማዕከሉ ዋነኛ ችግር መሆኑን በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል፡፡

በማዕከሉ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ በካንሰር የተያዙ 700 የሚደርሱ ህጻናትና ልጆች መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማዕከሉ ህሙማንን ለመርዳት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ተናግረው ከዚህ ጎን ለጎንም ማዕከሉ ያለበትን ችግሮች ለማየት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ችግሩን ለመከላከል መረባረብ እንዳለበት የሚያመላክት መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዝዳንቷ በአንድነት ከተንቀሳቀስን ችግሮቹ ከአቅማችን በላይ ሊሆኑ አይችሉም ብለዋል፡፡ 

ቀጣዩን የገና በዓል በማስመልከትም ፕሬዝደንቷ ለልጆቹ ስጦታ አበርክተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት)