የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በከተማ ልማትና ቤቶች ግንባታ ዙሪያ ከዲያስፖራዎች ጋር ውይይት አደረገ

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በከተማ ልማትና ቤቶች ግንባታ ዙሪያ ከዲያስፖራዎች እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አላላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ጋር በመተባበር “የዲያስፖራው ተሳትፎ ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው የተዘጋጀው ።

 የውይይት መድረኩም በተለያዩ ሀገራት ለረዥም ዓመታት በውጭ ሃገራት የኖሩ እና የተለያዩ ልምዶችና ሃብት ያካበቱ ዲያስፖራ ባለሃብቶች ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው በሃገራቸው እድገት የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማድረግ ያለመ መሆኑን የመድረኩ አዘጋጆች ገልጸዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ዲያስፖራዎች በበኩላቸው ወደ ሀገራቸው ገብተው በሚፈልጉት ዘርፍ ላይ ለመሰማራት ጥሪ ቀርቦላቸው ወደ ሃገራቸው እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ከመኖሪያ ቤት እና ከኢንቨስትመንት መሬት ጋር በተያያዘ ችግር እንደገጠማቸው ነው በመደረኩ ላይ አንስተዋል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎቹ  በሚፈልጉት ዘርፍ ሀገራቸውን የማልማት ፍላጎት ቢኖራቸውም በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ባለው ቢሮክራሲ ችግር አማካኝነት የሚጠበቅባቸውን ያህል አለማሳካታቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ልማት እና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ከዲያስፖራዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን ዲያስፖራዎቹ ያነሱት ጥያቄዎች ትክክል መሆናቸውን ገልጸው ቅሬታቸው ከዚህ በኋላ በየደረጃው ባለው መዋቅር አማካኝነት የሚፈታበት መንገድ እንደሚመቻችም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዲያስፖራዎቹ ከመኖሪያ ቤት ቁጠባ ጋር በተያያዘ ከሀገር ውስጥ ካሉ ዜጎች ጋር እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡