ዩኒቨርስቲው ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድቦ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየሠራ መሆኑን ገለጸ

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መድበው በዳውሮና ወላይታ ዞኖች ላይ የማህበርሰብ አቀፍ ቴክኖሎጂ ሽግግር እና ሌሎች ዘርፎች ላይ እየሠራ መሆኑን ገልጿል፡፡

በዩኒቨርስቲ የምርምርና ማህበርሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ታከለ ታደሰ 49 ተመራማሪዎች በተለያዩ ዘርፎች ህብረተሰቡን ሊያግዙ የሚችሉ የጥናት ውጤቶችን ለማዘጋጀት ከዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች ጋር ውል ገብተው እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው በሶዶ ከተማ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድን ዘመናዊ ለማድረግ ከከተማ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ህብረተሰቡ የሚጠቀመውን የባህላዊ ህክምና ወደ ዘመናዊ ለማድረግ በተጨማሪም ከዳውሮና ወላይታ ለተመረጡ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱን ለማዘመን የሚያግዙ የዕውቀት ሽግግሮችንና የትምህርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

የወላይታ ዩኒቨርስቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶክተር ወንድሙ ወልዴ በበኩላቸው ተቋሙ የራሱን የውስጥ አቅም ለማሳደግ ከውጭ ሀገራት ዩኒቨርስቲዎች ጋር እና በሀገር ውስጥ ካሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ተደርጎ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡