13ኛው “የጤናማ እናትነት” በዓል እየተከበረ መሆኑ ተገለጸ

13ኛው የጤናማ እናትነት በዓል ከጥር 1 እስከ ጥር 30 2011 ዓ.ም. በሃገር አቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች፣ ዞኖች፣ ወረዳዎች እንዲሁም ጤና ተቋማት ይከበራል፡፡

ዘንድሮ ለ13ጊዜ የሚከበረዉን የጤናማ እናትነት ወር አስመልክቶ የኢፌዲሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የጤና ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደተናገሩት ምንም እንኳን የእናቶች ሞት በሃገር ደረጃ በተሰጠዉ ትኩረት እና በተከናወኑ በርካታ ተግባራት ለዉጥ የተመዘገበበት ቢሆንም አሁንም ድረስ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በማደግ ላይ ባሉ አገራት በወሊድ እና ከወሊድ ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች እናቶች ህይወታቸዉን ያጣሉ፡፡

ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነዉ የችግሩ መንስኤ የደም መፍሰስ ችግር እንደሆነም ተገልጿል፡፡  

በዓሉ “በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተዉን የእናቶች ሞት በጋራ እንከላከል!” በሚል መሪ ቃል ነዉ እየተከበረ የሚገኘዉ፡፡

ሁሉም ባለድርሻ አካላት የእናቶችን ሞትና ህመም ለመቀነስ በሚደረገዉ ሀገራዊ ጥረት ዉስጥ የበኩላቸዉን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ማነቃቃት የበዓሉ ቀዳሚ አላማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአለም የጤና ድርጅት እ.ኤ.አ በ2016 ያወጣዉ ሪፖርት እንደሚያሳየዉ በአለም ወደ 303 ሺህ እናቶች ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር በተያያዘ ህይወታቸዉን አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያም እ.ኤ.አ በ1990 ከ100 ሺህ እናቶች ዉስጥ 1ሺህ 250 ሞት ሲያጋጥማቸዉ የቆየ ሲሆን በተሰሩ የተለያዩ ስራዎች ቁጥሩን ወደ 353 ዝቅ ማድረግ  መቻሉን  በጋዜጣዊ መግለጫዉ ተገልጿል፡፡