የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኤሌክትሪክ ኃይል አለመመጣጠን ምክንያት ለሚደርሱ ጉዳቶች ካሳ ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የከፍተኛ ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች  በኤሌክትሪክ ኃይል አለመመጣጠን ምክንያት እየደረሰባቸው ላለው ጉዳት  ካሳ  ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከአገሪቱ  የከፍተኛ  የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች  ጋር  በዛሬው ዕለት  በካፒታል  ሆቴል ውይይት አድርጓል ።

በተካሄደው ውይይትም  የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች  በኃይል አለመመጣጠንና  መቆራረጥ  ምክንያት   የተለያዩ  የማምረቻ   ማሽኖቻቸው  እየተበላሹባቸው መሆኑን  በወይይቱ  ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ  ኃይል ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብርሃም በላይ በቅርቡ  በመብራት  መቆራረጥ  ምክንያት  የሚደርሰውን  ችግር  ለመቋቋም  ከከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች  ጋር  የዋስትና ውል  እንደሚገባም  ገልጸዋል ።

ኮርፖሬሽኑም   የኃይል  ተጠቃሚዎች  በኃይል አለመመጣጠን ምክንያት  የሚደርሱ ጉዳቶችን በጥናት  ላይ በተመሠረተ ሁኔታ  የካሳ  ክፍያን  ለመፈጸም  ዝግጁ  ስለመሆኑ ኃላፊው አመልክተዋል ።

በተለይ  የኢንዱስትሪ  ፓርኮች  እያጋጠማቸው  ያለው የኤሌክትሪክ  ኃይል መቆራረጥና  አለመመጣጠን  ችግር   የተከሰተው   የመብራት መሠረተ ልማትን  ከግምት ውስጥ  ባላስገባ  ሁኔታ   የኤሌክትሪክ  መሠረት ልማት ዝርጋታ  በመካሄዱ  መሆኑንም በወይይቱ ተመልክቷል ።