በዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ ቁሳቁስ መሟላት እንዳስደሰታቸው የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቴ ተማሪዎች ገለጹ

በዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ ቁሳቁስ መሟላት እንዳስደሰታቸው የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቴ ተማሪዎች ለዋልታ ቲቪ ገለጹ፡፡

እንደ ተማሪዎቹ ገለጻ ከዚህ ቀደም ዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ ቁሳቁስ ባለማሟላቱ ወደ ባህርዳር፣ ጎንደር እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለተግባር ልምምድ ይሄዱ ነበር፡፡

ተማሪዎቹ ለተግባር ልምምድ ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በሚሄዱበት ወቅት መምህራኖቻቸውም አብረው መጓዛቸው ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎት ቆይቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት ግን የላብራቶሪ ቁሳቁስ በመሟላታቸው ወደ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረግ ጉዞ ሙሉ በሙሉ እንደቀረ ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ግዜያቸውን እና ሙሉ አቅማቸውን በተረጋጋ መልኩ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ አስችሏቸዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው መምህራን በበኩላቸው የላብራቶሪ እቃዎች መሟላት ተማሪዎቹ በቲዮሪ ያገኙትን እውቀት በተግባር እንዲተረጉሙት እንደሚያስችላቸው ጠቁመዋል፡፡

ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሲወጡም የተሟላ እውቀት ይዘው ህዝባቸውን ማገልገል እንደሚያስችላቸውም መምህራኑ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም መምህራኑ ከማስተማር ስራው ጎን ለጎን የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እንዲያከናዉኑ ያግዛቸዋል፡፡

የሚዛን-ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ተሊል በበኩላው ዩኒቨርሲቲው የላብራቶሪ እቃዎችን ለማሟላት ከ 50 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ገልጸው ይህም ለትምህት ጥራትን በማረጋገጥ በኩል ትልቅ ድርሻ አለው ብለዋል፡፡