ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ ጋር ተወያዩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተባበሩት መንግስታት የአለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቤዝሊ ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡

የአለም የምግብ ድርጅት ኢትዮጵያን በምግብ ደህንነት፣ በተመጣጠነ ምግብና በአቅም ግንባታ ዘርፎች እንደሚረዳ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያስታወሱት ሲሆን የአለም የምግብ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቤዝሊ በበኩላቸው ለኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል ዶክተር አብይ አህመድ በዛሬው ዕለት ሁለተኛው የልማት አጋርነት  ውይይታቸውን ከግብርና ልማት አለም አቀፍ ፈንድ ፕሬዝዳንት ከሆኑትጊልበርት ሆዉንግቦ ጋር አካሂደዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፉት ጥቂት ወራት በአገሪቱ የተመዘገቡትን ለውጦች ለማምጣት ያሳዩትን ቆራጥነት አድንቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው የመስኖና የምግብ ዋስትና እንቅስቃሴዎችን ማጠናከር ላይ ትኩረት ሰጥተው ተወያይተዋል፡፡

የግብርና ልማት አለም አቀፍ ፈንድ በኢትዮጵያ የሚያደርገው ድጋፍ ከአፍሪካ ትልቁ ሲሆን በመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ በተለይም በአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ምርታማነት ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ሁለቱ ወገኖችም እገዛ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ለማሟላት በመካከለኛ ደረጃ የመስኖና የገጠር ፋይናንስ ፍሰትን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)