በአዲስ አበባ ጉርድ ሾላ አከባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች በህገ ወጥ መልኩ ቤታችን ፈርሶብናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት በተለምዶ ጉርድ ሾላ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች ቅደመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጥ በህገ ወጥ መልኩ ህጋዊ ቤታችን ፈርሶብናል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡

ቅሬታቸውን ለዋልታ የገለጹት ነዋሪዎቹ የአየር ካርታም ሆነ ህጋዊ የግንባታ ፈቃድ እንዳላቸውና ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ጊዜም ሆነ ማስጠንቀቂያ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ከወረዳው ጋር ለኮብል ስቶን መንገድ ሥራ የስምንት ሜትር ስፋት ቦታ መስማማታቸውን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ እያንዳንዳቸው የ3 ሺህ ብር መዋጮ ለመንገድ ሥራ ቢያዋጡም መንገዱ ሳይሰራ አምስት አመት መቆየቱንና ያዋጡትም ገንዘብ የደረሰበት ሳይታወቅ ቀርተዋል ብለዋል፡፡

በህጉ መሰረት ህጋዊ ካርታም ሆነ ቤት ያለው ንብረት መንግስት ሲያፈርስ የካሳ ክፍያ እንደሚከፍል የሚታወቅ ቢሆንም የኛ ንብረት ሲወድም ምንም የካሳ ክፍያ አልተሠጠንም ሲሉም ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን አስመልክቶ ዋልታ ያነጋገረው የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ምክትል ስራአስፈፃሚ አቶ ፈለቀ ኢሳያስ  የአካባቢውን ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ማወያየቱንና ከመግባባት ላይ በመድረስ ቤታቸውን እንዳፈረሰ ገልጸዋል፡፡

ወረዳው ለእያንዳንዱ ነዋሪ በስማቸው ቤት ለቤት ተዘዋውሮ ደብዳቤ ከመስጠት ባለፈ ቅድመ ማስጠነቀቂያ በመስጠት ህጉን ተከትሎ ማፍረሱን ምክትል ስራአስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

በህገወጥ መንገድ የፈረሰባቸው ካሉ መረጃቸውን በማየት ካሳውን ለመክፈል ወረዳው ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡