የመጀመሪያው የሚዲያ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

የመጀመሪያ የሆነው የሚዲያ ኤክስፖ በአዲስ አበባ ኤግዝቢሽን ማዕከል ከጥር 17 እስከ 19፤2011 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የሚዲያ ኤክስፖ በሆም ፕሮሞሽን አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን የኤክስፖው ዓላማ በሚመለከት አዘጋጆቹ ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በሚዲዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ለመፍጠርና የልውውጥ ማዕከል ለማድረግ ያለመ መሆኑን የገለጹት አዘጋጆቹ ኤክስፖው በሚዲዎች የእርስ በርስ ትስስር እንዲኖር በማድረግ የተለያዩ የገበያ ዕድሎችን ለመፍጠር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሚዲዎች ዘንድ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ትውውቅ አንዲኖር የማድረግ ዓላማ እንዳለውም በመግለጫው ተገልጿል፡፡

ለኤክስፖው የ9 ካሬሜትር ቦታ በመንግስት በነፃ ለሚዲዎች እንደተሠጠና ከዛ ያለፈው ቦታ  በተወሰነ ክፍያ የሚሠጥ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል፡፡

የሚዲያ ኤክስፖው በሚቀጥለው አመትም እንደሚዘጋጅና የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርጎበት የዓለምአቀፍ ሚዲዎች እንዲሳተፉ በማድረግ የልምድ ልውውጥ የሚደረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በኤክስፖው ከ70 በላይ የአገር ውስጥ ሚዲያ ዘር አካላት ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡