ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጎለብት ተማሪዎች ለሰላም ትኩረት ሊሰጡ ይገባል-የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲጎለብት ተማሪዎች ቅድሚያ ለሰላም ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡

ለዋልታ አስተያየታቸውን የሠጡት የዩኒቨርስቲው የሰላም ፎረም አባል ተማሪዎች በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን በሁሉም ሰው ልብና አዕምሮ ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ተማሪዎቹ  የማህበራዊ ሚዲያ በመከታተል ጊዜን ከማባከን ይልቅ ለመጡበት ዓላማ በመቆም ለሚያስተምራቸው  ቤተሰብና አገር በማሰብ ትምህርት ላይ ትኩረት ሰጥተው ሰላም እንዲሰፍን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተማሪዎቹ አክለው ገልጸዋል፡፡

በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር መሐመድ አወል የተለያዩ አሉታዊ አጀንዳዎች ያላቸው አካላት ተማሪዎችን የተልዕኮ ማስፈጸሚያና መሸጋገሪያ ድልድይ በማድረግ ሰላም  በማሳጣት ፣ በመንግስት ላይ ጫና ለመፍጠር እንደሚፈልጉ በመግለጽ ተማሪዎችን  ለመጠቀም የሚፈልጉት አካላት ከድርጊታቸውን  እንዲቆጠቡ  ለማድረግ የድርሻቸውን  እንዲወጡ ጥሪ አቅበዋል ፡፡

ተማሪዎቹ ዛሬ ካሉበት ደረጃ ተሻግረው ነገ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ የሚቀመጡ በመሆናቸው በዩኒቨርስቲ ያለውን ህብረ ብሔራዊነት በመጠቀም እርስ በርስ በመተዋወቅ፣ በመተባበርና በመረዳዳት ሊማሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡