የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደርና የመሰረተልማት ችግሮች መቀረፍ እንደሚገባቸው ተጠቆመ

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉት የመልካም አስተደደር የመሰረተልማት ችግሮች በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ እንቅፋት በመሆናቸው መቀረፍ እንደሚገባቸው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰዉ ሀብት ልማትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ።

ቋሚ ኮሚቴዉ በወቅታዊ የዩኒቨርሲቲዎች የመማርማስተማርና የጸጥታ ሁኔታ ዙሪያ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል።  

በዉይይቱም ቋሚ ኮሚቴዉ የዩኒቨርሲቲዎቹን የመማርማስተማርና የሰላም ሁኔታ ዙሪያ በመስክ ምልከታ ያስተዋላቸዉን 31 የግኝት ነጥቦች በዝርዝር አቅርቧል።

ኮሚቴዉ በጎንደር፣ በሰላሌ እና በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች የመስክ ምልከታ የደረገ ሲሆን፣ በምልከታዉም በተለይም በአዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የዉሃ አቅርቦት፣ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥና የመማሪያ መሳሪያዎች አለመሟላት ችግሮችን እንዳስተዋለ ገልጿል።

እነዚህ ችግሮቸ የመማርማስተማር ሒደቱን ከማስተጓጎልና በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደራቸዉም ባለፈ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሚስተዋሉት የሰላምና ጸጥታ ችግሮች ምክንያት መሆናቸዉንም የቋሚ ኮሚቴዉ አባላት አንስተዋል።

በተጨማሪም የግንባታ ፕሮጄክቶች መጓተትና ሌሎች የአስተዳደር ክፍተቶችም በዩኒቨርሲቲዎቹ የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸዉ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲዎች በቅርቡ ተከስተዉ የነበሩ የፀጥታ ችግሮች መቀረፋቸዉንና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ዉጪ አብዛኞቹ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ የመማርማስተማር ሒደታቸውን በማከናወን ላይ እንደሆኑ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ተናግረዋል።