በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ህጋዊ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር ገለጸ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በህገ-ወጥ የጎዳና  ንግድ ላይ  የተሰማሩ ነጋዴዎች ወደ ህጋዊ ንግድ እንዲገቡ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 27 ሺህ ስራ አጥ ወጣቶች እና ከዚህ ቀደም በህገወጥ የጎዳና ንግድ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ነጋዴዎችን ወደ ህጋዊ ንግድ እንዲገቡ ለማድረግ እየሠራ ይገኛል።

ከተማ አስተዳደሩ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች ለሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች እና ህገ ወጥ ነጋዴዎች የመሥሪያ ቦታ እየሠጠ  መሆኑንም ገልጿል።

 ለዋልታ  ቴሌቭዥን አስተያየታቸውን የሠጡት  የንግድ  ቦታ  የተረከቡ  ነዋሪዎች እንደሚገልጹት በአስተዳደሩ የተሠጣቸው የመሥሪያ ቦታዎቹ አመቺ  ያልሆኑና ለመኪና አደጋ ሊያጋልጡ እንደሚችሉ  ይናገራሉ።

በተጨማሪም የንግድ ቦታዎቹ የከተማዋ የገጽታ ከማበላሸቱም ባሻገር፣  የከተማዋን የዕድገት ደረጃ የማይመጥን ፣  የቱሪዝም ኢንዲስትሪው ላይ ተፅእኖ የሚፈጥር በመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባ የኢንተር ኮንትኔታል ሆቴል ሥራ አስኪያጅ አሳስበዋል።