በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብልሹ አሠራርን በመቃወማቸው ምክንያት ከሥራ ገበታቸው መታገዳቸውን ካህናት ገለጹ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ብልሹ አሠራርን በመቃወማቸው ምክንያት  ከስራ ገበታቸው  በህገ ወጥ መንገድ የተባረሩ መሆኑን  ለዋልታ  ቅሬታቸውን  ያቀረቡ 320 የሚሆኑ ካህናትና የአስተዳደር ሠራተኞች ገለጹ ፡፡

በሀገረ ስብከቱ እያገለገሉ ያሉ ካህናትና የአስተዳደር ሠራተኞች ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ስራችን እንደንመለስ ቢወስንልንም ከተባረርነው 320  ሠራተኞች አንድም ወደ ሥራ ገበታው የተመለሰ ሰው የለም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፅ/ቤት ሃለፊ እንዲሁም እንዲሁም የደቡብ ሸዋና ኬንያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ችግሩ የተፈጠረዉ የሲኖዶሱ ዉሳኔ ያስፈፅማል ተብሎ የተመለመለዉ አመራር ውሳኔው ተግባራዊ ባለማድረግ ነዉ ብለዋል፡፡

ቅሬታው አግባብ መሆኑን ያመነው የቅዱስ ሲኖዶስ ፅ/ቤት ያለ አግባብ የተባረሩትን ካህናት ወደ ስራቸው እንዲመልሱ እና በሀገረ ስብከቱ ያለውን ሁለንተናዊ ችግር ለመቅረፍ የተመደቡት አዳዲስ  አመራሮች  ከቀደመው አመራር የተሻለ ለውጥ  ለማምጣት ዝግጁ ባለመሆናቸው  መጉላላቱ መፈጠሩን አስታውቋል፡፡

በሀገረ ስብከቱ የሚታየው ቅጥ ያጣ ብልሹ አሠራር የሚቀረፍበት መንገድ እየተፈለገ ነዉ ፤ችግሩን በመቅረፍ አስተዳደሩ ፈር እንዲይዝ ይሠራልም ብለዋል፡፡

በሃገረ ስብከቱ ካሉት 54 ሀገረ ስብከቶች የአዲስ አበባ እንዲህ በበዛ ችግር ውስጥ የገባው ተጠሪነቱ ለሊቀ ፓትሪያሊኩ በመሆኑና ፓትሪያሊኩ የሃገረ ስብከቱን የእለት ተዕለት ተግባር መቆጣጠር ባለመቻላቸዉ ነዉ ብሏል፡፡

በተጨማሪም ለሲኖዶሱ ሰራተኞቹ እንደተመለሱ የሀሰት ሪፖርት ያቀረቡት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አመራሮች አሁን ከሀላፊነታቸው መነሳታቸው የተገለፀ ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜ የተሾሙት አመራሮች ችግሩን ቢበዛ በአንድ ሳምንት ውስጥ መፍትሄ ይሠጡታል ተብሏል፡፡