በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ ከሜክሲኮ ወደ ቄራ በሚወስደው ሥፍራ አካባቢ የፅዳት ዘመቻ አካሂዷል፡፡

ፅዳቱ የተካሄደበት ቦታ በ2009 ዓ.ም የልማት ተነሽዎች ከቦታው ተነስተው ለኳታር ባለሀብቶች የተሰጠ ቢሆንም አልሚዎቹ በስፍራው ገብተው ስራ ባለመጀመራቸው ምክንያት የአካባቢው ነዋሪዎች ለጸጥታ ችግር መጋለጣቸውን ገልጸዋል፡፡

የፅዳት ዘመቻው ዓላማም  በስፍራው ላይ የበቀለውን ቁጥቋጦ በመመንጠር ከወንጀለኞች ነፃ ለማድረግ ነውም ተብሏል፡፡

በዘመቻው ላይ የተገኙት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምክትል ሥራአስፈፃሚ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በከተማው ለልማት ተብለው የታጠሩት ቦታዎች በተግባር ላይ ባለመዋላቸው ለተለያዩ እኩይ ዓላማ መዋሉ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች ለልማት የተሰጡ ቦታዎችን ከተማ አስተዳደሩ በመቆጣጠር በፍጥነት ወደ ስራ እንዲያስገባና ለአልሚዎች ማሳለፍ እንደሚገባ ወይዘሮ ሊዲያ ጠይቀዋል፡፡