በምዕራብ ጎንደር ተከስቶ በነበረው ግጭት ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ 838 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ተከስቶ በነበረው ግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ወደ ሱዳን ተሰደው የነበሩ 838 ኢትዮጵውያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

ካርቱም በሚገኝው የኤፌዴሪ ኤምባሲና የገዳሪፍ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ከሱዳን የስደተኞች ኮሚሽን እና የመንግስታቱ ድርጅት የፍልሰተኞች ድርጅት አይ ኦ ኤም ጋር በመሆን ዜጎቹ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጓል።

በሱዳን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽፈራው ጃርሶ እና በገዳሪፍ የኢፌዴሪ ቆንሱል ጄኔራል አምባሳደር አለማየሁ ሰዋገኝ ከሱዳን የሚመለከታቸው አካላት ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በሸገርአብ ስደተኞች ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ቀሪ 500 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቅርቡ ከሚመለከታቸው የሁለቱ አገራት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋልም ተብሏል።

የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በቅርቡ በኢትዮ-ሱዳን የጋራ የኢኮኖሚ ኮሚቴ ስብሰባ ጎን ለጎን ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር እና ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዩሲፍ ኪቢር ጋር ባደረጉት ውይይት ወቅት በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች እና በእስር ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ጉዳይን በማንሳት  ወደ አገራቸው እዲመለሱ እና በእስር ላይ የሚገኙት ደግሞ እንዲፈቱ ከስምምነት መደረሱ ይታወሳል። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት)