የህዝብና ቤት ቆጠራው እንዲራዘም ኮሚሽኑ የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ

የህዝብና ቤት ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም የቆጠራ ኮሚሽኑ በመወሰን የውሳኔ ሃሳቡን ለተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲቀርብ መላኩን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ገለፀ።

ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ የህዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን ዛሬ መጋቢት 7 ቀን 2011 ባካሄደው ስብሰባ 4ኛዉን የህዝብና ቤት ቆጠራ ለማካሄድ የተደረገዉን ዝግጅት በመገምገም የዉሳኔ ሃሳቦች ማሳለፉን አመልክቷል።

በዚህም መሠረት:-

  • የሕዝብና ቤት ቆጠራው እንዲቀጥል በቴክኒክ ደረጃ በቂ ዝግጅት የተደረገ መሆኑንና ኮሚሽኑና ማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ሰፊ ስራ ያከናወኑ መሆኑን፣
  • የካርታ እና ተያያዥ ስራዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን፣
  • ሌሎች ዝግጅቶችም እየተደረጉ መሆኑን ግንዛቤ ወስዶ የቆጠራውን አላማና ግብ በአስተማማኝ ሁኔታ ለማሳካት የሚያስችሉ ተግባራት የተሟሉ ባለመሆናቸው ማለትም በየአካባቢው ለስራው መሳካት በተገቢው ሁኔታ መጠናቀቅ የሚገባቸው ተግባራት ባለመጠናቀቃቸው እና ተጨማሪ ግዜ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣
  • ምንም አንኳን ለቆጠራ የቀሩት ቀናት ጥቂት ቢሆንም በተለያዩ ግጭቶች ምክንያት የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ወገኖች ወደነበሩበት ቀዬ የመመለሱ ስራ በበቂ ሁኔታ ባለመሰራቱ አሁንም ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ በመሆኑ እነዚህ ወገኖች ትርጉም ባለው ደረጃ ወደ ነበሩበት ቦታ እስኪመለሱ ድረስ ተጨማሪ ጊዜ በማስፈለጉ ቆጠራው እንዲራዘም የውሳኔ ሃሳቡን ለተወካዮችና ለፌዴሬሽን ምክር ቤቶች እንዲቀርብ በአብላጫ ድምፅ መወሰኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።