ኢትዮጵያ በብሪታኒያ ብሄራዊ ጦር ሙዚየም የነበረውን የአጼ ቴዎድሮስ ፀጉር ተረከበች

ኢትዮጵያ በብሪታኒያ ብሄራዊ ጦር ሙዚየም ውስጥ የነበረውን የአጼ ቴዎድሮስ ፀጉር ተረክባለች።

በብሪታኒያ ብሄራዊ ጦር ሙዚየም የነበረውን የአጼ ቴዎድሮስ ፀጉርንም የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በለንደን ተገኝተው ተረክበዋል።

ሚንስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ የብሪታኒያ መንግስት ይህን ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፍ ምላሽ በመስጠቱ አመስግነዋል።

በለንደን የሚገኙት ቅርሶች ከእንግሊዞች ይልቅ ለእኛ በጣም የሚጠቅሙን የእድገትና ስልጣኔ ምንጮችና መሰረቶች ናቸውና እንዲመለሱልን ጥረት ማድረግ እንቀጥላለን ሲሉም ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ መንግስት ቅርሶችን የማስመለስ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በለንደን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከኤምባሲው ጋር በመሆን በአንድነት በግለሰብ እጅ እና በተለያዩ ተቋማት የሚገኙ ቅርሶችን ከመለየት ጀምሮ እንዲመለሱ የማድረጉን ስራን አጠናክረው እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና በባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው የሚመራ የኢትዮጵያ የልኡካን በድን በለንደን በሚገኘውን የብሪታኒያ ብሄራዊ ሙዚየምን ጉብኝት አድርጓል።

በዚሁ ወቅት ከሙዚየሙ ሃላፊዎች ጋር ውይይት ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት፥ ሙዚየሙ በአለም ስመ ጥርና የተደራጀ መሆኑን በመጠቆም በሙዚየም ግንባታና አደረጃጀት ላይ አብሮ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ሚንስትር ዶክተር ሂሩት አክለውም፥ በሙዚየሙ የሚገኙ ፅላቶች ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ልዩ ክብርና ቦታ ያላቸው ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙባቸው ህያው በመሆናቸው ወደ ትክክለኛ ቦታቸው እንዲመለሱ ጠይቀዋል።

የሙዚየሙ ሀላፊዎች ሀሳቡን እንደሚጋሩትና የህግ ጉዳይ ሆኖ መወሰን ባይችሉም በሚቀጥለው ሃምሌ ላይ በሚኖራቸው የሀገሪቱ ሙዚየም ባለአደራ ቦርድ አቅርበው ምላሽ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። (ምንጭ ፡- ኤፍ.ቢ.ሲ)