የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር (ቁንዳላ) በብሄራዊ ሙዚየም አቀባበል ተደረገለት

የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር(ቁንዳላ) አቀባበል ስነ ስርዓት ዛሬ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ሙዚየም ተካሄደ።

የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚንስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው በስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር የብሪታኒያ መንግስት ይህን ታሪካዊ ውሳኔ በማሳለፍ የአፄ ቴዎድሮስን ፀጉር በመመለሱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በለንደን የሚገኙት የኢትዮጵያ ቅርሶች ከእንግሊዞች ይልቅ ለእኛ በጣም የሚጠቅሙን የእድገትና ስልጣኔ ምንጮችና መሰረቶች በመሆናቸው እንዲመለሱልን ጥረት ማድረግ እንቀጥላለን ሲሉም ገልፀዋል።

የኢፌዴሪ መንግስት በውጭ አገራት የሚገኙ ቅርሶችን የማስመለስ ጥያቄውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጿል።

ከ150 ዓመታት በላይ በብሪታኒያ ብሄራዊ ጦር ሙዚየም የነበረውን የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉርን ሚንስትሯ በለንደን ተገኝተው መጋቢት 11፣ 2011 ዓ.ም. በይፋ መረከባቸው የሚታወስ ነው።

በአቀባበል ስነ ስርዓቱ ላይ አርበኞች፣ አርቲስቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።