በአዲስ አበባ ከ3 ሺህ በላይ ዜጎች ከጎዳና መነሳታቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ 3 ሺህ 147 ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችን ከጎዳና ላይ በማንሳት በ8 ማዕከላት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን የአዲስ አበባ ማህበራዊ ትረስት ፈንድ አስታወቀ፡፡

የትረስት ፈንዱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ሁነኛው አየለ መንግስት ለመነሻነት 92 ሚሊዮን ብር መድቦ ስራ መጀመሩን ገልጸው በዚህ ዓመት 5 ሺህ የሚጠጉ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ ማዕከሉ ለማስገባት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በከተማዋ ከ50 ሺህ በላይ የጎዳና ተዳዳሪዎች አሉ ያሉት አቶ ሁነኛው ከጎዳና የማንሳቱ ስራ ከፍተኛ ሀብት የሚፈልግ በመሆኑ ህብረተሰቡም ሆነ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

ከጎዳና ወደ ማዕከሉ የገቡት ልጆች በተለያዩ ሱሶች የቆዩ ከመሆናቸው አንፃር ፍላጎታቸውን ማሟላት አስቸጋሪ መሆኑን ተቁመው፣ መረጃዎችን የማደራጀት ስራና ወደ መጡበት አካባቢ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ክልሎች የሚያሳዩት ፍላጎት ዝቅተኛ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

ዋልታ ቴሌቪዥን  ባደረገው ቅኝት በመስቀል አደባባይ ያነጋገራቸው የጎዳና ተዳዳሪዎች አዲስ በተቋቋመው ማህበራዊ ትረስት ፈንድ አማካኝነት ወደ ማገገሚያ ማዕከላት ለመግባት ፍላጎት እንዳላቸው እና ቀጣዩን ዙር እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ አስተያየታቸውን ለዋልታ የሰጡ የማህበረሰብ ክፍሎች በበኩላቸው የጎዳና ልጆቹን ለመደገፍ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽዖ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረው የበኩላቸውን ድጋፍ የስልክ የጽሑፍ መልዕክት 6400 A ብለው በመላክ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡