በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተነሳው የሰደድ እሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ዋለ

የእሳት ቃጠሎ እዲፈጠር አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ 17 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ ኃላፊ አቶ አስቻለው ጋሻው ለኢዜአ እንደገለጹት በጎባና ዲንሾ ወረዳዎች ውስጥ ተከስቶ የነበረውን ሰደድ እሳት መቆጣጠር የተቻለው ትናንት ማምሻውን ነው፡፡

የፓርኩ ክልል በቀላሉና በፍጥነት በሚቀጣጠሉ አስታ የተባሉ የዛፍ ዝርያዎች መሸፈኑ እሳቱን በቀላሉ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ነው ያስታወሱት፡፡

እሳቱ ያደረሰው የጉዳት መጠን እንዳልታወቀ ያነሱት ኃላፊው የአስታ ዛፍ ዝርያዎችና ሌሎች ብዝሐ ህይወት ላይ ጉዳት መድረሱን አመልክተዋል፡፡

አቶ አስቻለው እንዳመለከቱት በህብረተሰቡ ተሳትፎና በአካባቢው ላይ በሚታየው ደመናማና ዝናባማ የአየር ፀባይ እሳቱ ለጊዜው ቢጠፋም ዳግም የመነሳት ባህሪ ስላለው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም /ዩኔስኮ/ በጊዜያዊ ቅርስነት የተመዘገበው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተለያዩ ብርቅዬ የዱር እንስሳትና አእዋፍ መገኛ ነው፡፡