ያለመኖሪያ ፈቃድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ 850 ኢትዮጵያዊያን ተመለሱ

​​​​​​ያለመኖሪያ ፈቃድ በሳኡዲ አረቢያ የሚኖሩ 850 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው እንደተመለሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ተመላሾቹ በሁለት ዙር የመጡ ሲሆን፣ የመጀመሪያዎቹ 445 ዜጎች ሚያዚያ 11 ቀን እና ቀሪዎቹ 405 ደግሞ ሚያዚያ 13/ 2011 ዓ.ም እንደተመለሱ ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት በራሳቸው ፈቃድ ሲሆን ቀይ ባህርን አቋርጠው በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳኡዲ አረቢያ ማቅናታቸውም ታውቋል።

ተመላሾቹ ወደ ሀገራቸው የገቡት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጅዳ በሚገኘው ቆንስላ ጽህፈት ቤት በኩል ከሳኡዲ አረቢያ መንግስትና ከዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት ጋር በተደረገ ትብብር ነው ተብሏል።

ኢትዮጵያዊያኑ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የቆንስላ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዮሃንስ ሾዴ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር በሳኡዲ አረቢያና በሌሎች አገራት ያለመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ ዜጎች በሰላም ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላልም ተብሏል።

(ምንጭ፡- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት)