3 ሺህ 500 አንባቢዎችን ማስተናገድ የሚችል ቤተ-መፃሕፍት ሊገነባ ነው

በአንድ ጊዜ 3 ሺህ 500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ ቤተ-መፃሕፍት በአዲስ አበባ ሊገነባ መሆኑን የከንቲባው ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በቀን እስከ 10 ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል የተባለው ይህ ቤተ-መፃሕፍት በአራት ኪሎ ከፓርላማ ፊት ለፊት እንደሚገነባ ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ቤተ-መፃሕፍቱ 38 ሺህ 687 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ለህፃናት እና ለአዋቂዎች የሚሆን የማንበቢያ እና አረንጓዴ ስፍራ ይኖረዋል፡፡

ለደራሲያን፣ ከያኒያን እና የጥበብ ሰዎች የሚሆን የመለማመጃ እና የቴአትር ማዕከላትንም ይይዛል፡፡

በተጨማሪም እያንዳንዳቸው ከ100 ሰው በላይ የመያዝ አቅም ያላቸው ሶስት የስብሰባ አዳራሾችን ያካትታል ተብሏል፡፡

ከ130 በላይ መኪኖችን የሚያስተናግድ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያም እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡

የቤተ-መፃሕፍቱ ግንባታ ተጠናቆ  በሁለት ዓመታት ውስጥ ወደ አገልግሎት እንደሚገባም ይጠበቃል፡፡

(የከንቲባ ጽ/ቤት)