የዳስ ውስጥ ትምህርትን ለማስቀረት መስራት ይኖርብናል – አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ

በኢትዮጵያ የዳስ ውስጥ ትምህርትን በማስቀረት ወደ ተሻለ የመማሪያ ክፍል ለማሸጋገር መሰራት እንዳለበት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ጥላየ ጌቴ ጋር ባደረገው ውይይት ተናገሯል። 

ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ከትምህርት ሚንስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ጋር የዳስ ትምህርት ቤቶች እንዴት ደረጃቸውን በጠበቁ ትምህርት ቤቶች መቀየር እንችላን በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ተወያይተዋል።

አትሌት ሀይሌ እንደሚለው ትምህርት ቤቶቹን ለመስራትና ማህበረሰቡን ለማገዝ ያነሳሳው እነዚህን የመማሪያ ዳሶች በቴሌቪዥን መስኮት መመልከቱ እንደሆነ ገልጿል።

በተመለከተው ነገር ማዘኑን የገለፀው አትሌት ሀይሌ የኔ አንድ ትምህርት ቤት መስራት ብቻ በቂ አይደለም በሀገራችን ያሉትን የዳስ ትምህርት ቤቶች ሁሉም ሊረባረብ ይገባልም ነው ያለው፡፡

አትሌት ኃይሌ እነዚህን ትምህርት ቤቶች ለመስራት ፈቃደኛ በመሆኑ የትምህርት ሚንስትሩ አድንቀው እንደሱ አይነት ታዋቂ ሰዎች በእንዲህ አይነቱ ተግባር መሳተፍና መደገፍ አለባቸው ብለዋል።

መካከለኛ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለመመደብ እየሰራች ባለች ሀገር እንደነዚህ አይነት ትምህርት ቤቶች ማየት እጅጉን ያማል ያሉት ሚንስትሩ፤  በርካታ ችግሮች አሉብን ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መስራት ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የዳስ ትምህርት ቤቶቹን ለመቀየር የቀዳማዊት እመቤት ቢሮና አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ፈቃደኝነታቸውን ያሳዩ ሲሆን በተለይ አትሌት ሀይሌ በየአመቱ ከሚዘጋጀው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሚሰበሰበው ገቢ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ተሰርተው እስኪያልቁ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግሯል።

አትሌት ሀይሌ በዋግ ኸምራ ብሄረሰብ ዞን በፃግብጂ ወረዳ የሚገኝን አንድ ትምህርት ቤት እስከ መጪው መስከረም 2012 ዓ.ም ሰርቶ እንደሚያስረክብም ነው የገለፀው።

ዋልታ ቴሌቪዥን ከአንድ ወር በፊት የእነዚህን የዳስ ትምህርት ቤቶች ችግርና የህብረተሰቡን ቅሬታ ማቅረቡ ይታወሳል።