የገንዘብ እጥረት ያለባቸው የኩላሊት ህመምተኞች የእጥበት ወጪያቸው ተሸፈነ

የገንዘብ እጥረት ላለባቸው ለተወሰኑ የኩላሊት ህመምተኞች የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ15 ቀን እስከ አንድ ወር የሚደርስ የእጥበት ወጪያቸው ተሸፈነ፡፡

ወጪውን የሸፈኑት ሞት በኩላሊት ይብቃ ማህበርና የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የማህበሩ ሥራአስኪያጅ ኢዮብ ወልደሚካኤል ድጋፍ የተደረገላቸው በዘውድቱ ሆስፒታል፣ ሚኒልክ ሆስፒታል፣ አዳማ፣ ሐዋሳ እና ባህርዳር የሚገኙ ህመምተኞችና የማህበሩ አባላት ሲሆኑ፣ ሀብት ንብረታቸውን ለህክምና ሽጠው የጨረሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አብዛኞቹ የማህበሩ አባላት ምንም ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ለኩላሊት እጥበትና ለመድኃኒት የሚያወጡትን ወጪ ለመሸፈን ከቤተሰብና ዘመድ አዝማድ በየጊዜው ድጋፍ ለመጠየቅ ተገደዋል ብለዋል፡፡

በሳምንት ሶስት ጊዜ እጥበቱን ለማከናወን ያልቻሉ የኩላሊት ህመምተኞች ለከፋ ችግርና ሞት መዳረጋቸውን የገለጹት አቶ ኢዮብ አሁን የተደረገላቸው ወጪያቸውን የመሸፈን ሥራ ለህመምተኞቹ ትልቅ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በበኩሉ ለኩላሊት ህመምተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡  

ህመምተኞች ለተደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ሌሎች ክፍለ ከተሞችም የአቃቂ ቃሊቲውን ፈለግ እንዲከተሉ ጠይቀዋል፡፡