የሙስሊም ተቋማዊ አንድነት የጋራ ምክር ቤት ኮሚቴና የጋራ ዑለማዎችን ያሳተፈ ጉባኤ ሊካሄድ ነው

የሙስሊም ተቋማዊ አንድነት የጋራ ምክር ቤት ኮሚቴ የጋራ ዑለማዎች ምክር ቤት ለማቋቋም የሚያስችል ጉባዔ ሊያካሂድ ነው፡፡

ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ ሚያዚያ 23/2011 ከሁሉም የሙስሊም ህብረተሰብ የተወከሉ ዑለማዎችና ምሁራን የሚሳተፉበት መድረክ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ብሏል፡፡

በጉባዔው ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጀምሮ ባለፉት አስር ወራት  ያከናወናቸውን ተግባራት ጨምሮ የሙስሊሙን አንድነት ለመመለስ የጋራ የዑለማዎች ምክር ቤት እንዲቋቋም ይደረጋል ተብሏል፡፡

የሙስሊም ተቋማዊ አንድነት የጋራ ምክር ቤት ኮሚቴ ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲህ ሀጅ ዑመር ኢድሪስ እንዳሉት ኮሚቴው ባለፉት ወራት የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት በሚመልሱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር መስራቱን ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮሚቴው ባለፉት ወራት መጅሊሱ የሚመራበትን የህግ ጉዳዮች፣ የመዋቅርና በእምነቱ ውስጥ ያሉ የአተረጓጎም ልዩነቶችን በተመለከተ ሰነድ መዘጋጀቱን የገለፁት የኮሚቴው ፀሐፊ ዑስታዝ ካሚል ሸምሱ ሚያዚያ 23 በሸራተን ሆቴል በሚደረገው ጉባዔ ሰነዱ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ብለዋል፡፡

በጉባዔው የጋራ የዑለማ ምክር ቤት እና የጋራ ጊዜያዊ ባለአደራ ምክር ቤት እንደሚቋቋም ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ኮሚቴው ከተቋቋመ ጀምሮ ህዝበሙስሊሙን አንድ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሲሰራ የቆየ መሆኑ በመግለጫው የተነሳ ሲሆን፣ በአንዳንድ ወገኖች የጋራ መግባባት እንደሌለ ተደርጎ የሚነገረው ወሬ ትክክል አለመሆኑን ኮሚቴው በመግለጫው ጠቅሷል፡፡