የስቅለት በዓል በመላው አለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ዘንድ በድምቀት ይከበራል

የእየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል ኢትዮጵያን ጨምሮ በእስራኤል፤ ጀርመን፤ ስፔን፤ ጣልያን፤ ጃማይካ፤ በእንግሊዝና በመካከለኛው አሜሪካ በተለያዩ ክንውኖች ታስቦ ይውላል፡፡

በመላው አለም የሚገኙ ክርስቲያኖችም እለቱን እንደየ ወጋቸው እና የሃይማኖት ስርዓታቸው ያደምቁታል፤ ያስታውሱታልም፡፡

እየሩሳሌም የክርስቶስ ስቅለት የተካሄደበት ቦታ እንደመሆኗ በአሉ መንፈሳዊና ልማዳዊ በሆኑ ክንውኖች ይከበራል፡፡

ክርስቶስ በእየሩሳሌም መስቀል ተሸክሞ እንደተጓዘበትና ስቃይና መከራ እንደተቀበለበት በሚታመንበት መንገድ ምዕመናን መስቀል ተሸክመው በመጓዝ ስቅለትን ያከብራሉ ፡፡

በጀርመን የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ዘንድ እየሱስ ክርስቶስ ነፍሱን የሰዋበት ሰዓት ይታሰባል።

በአብያተ ክርስትያናት እየሱስ ክርስቶስ እስከ ተሰቀለበት ጊዜ ያለው ታሪክ ከመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ ይነበባል። ፀሎት ይደረጋል መዝሙር ይዘመራል።

በርካታ ጣልያናውያን ስቅለትን ለማሰብ በአብያተ ክርስትያናት ይሰባሰባሉ፡፡ ጣልያውያን ዕለቱን በጾም ያሳልፋሉ ወይንም የአሳ ተዋጽዖዎችን ብቻ ይመገባሉ፡፡

የስቅለት በአል በጀማይካ ልዩ በሆነ ክንውን ታስቦ ይውላል፡፡ አርብ ዕለት ጠዋት ጸሀይ ከመውጣቱ በፊት እንቁላሎችን በመስበር ያከብሩታል፡፡ እንቁላሉን ከሰበሩ በኋላ ነጩን ክፍል ከአስኳሉ በመለየት በብርጭቆ ውስጥ ያስቀምጡታል በብርጭቆ የተቀመጠው የእንቁላሉ ነጩ ክፍል ጸሀይ ካገኘው በኃላ የተለየ ምስል ያሳያል የሚል እምነት አላቸው፡፡

ቀደምት የጃማይካ አባቶች ይህ በብርጭቆ ውስጥ የሚታየው ምስል ሰዎች እንዴት እንደሚሞቱ የሚያሳይ ነው የሚል እምነት እንዳላቸውም ይገለጻል፡፡

በመካከለኛው አሜሪካ እንደ ሆንዱራስ፤ ኤል ሳልቫዶር፤ ጓቲማላ እና ሌሎች ሀገራት የስቅለት በአልን በተለያዩ የስነ ጥበብ ስራዎች አስበው ይውላሉ፡፡ በጎዳናዎች ላይ የእየሱስ ክርስቶስን ምስል በመሳል ያከብሩታል፡፡ እለቱ በቱርክ፣ ሩሲያ፣ ፊሊፒንስ፣ ግሪክ፣ ህንድ፣ ግብጽ እና ሌሎች የዓለም ሃገራት የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድም በተለያዩ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ስርዓቶች በድምቀት ይከበራል፡፡