ጣሊያን የአክሱም ሐውልቶችን ለመጠገን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታወቀች

የጣሊያን መንግስት የአክሱም ሐውልቶችን ለመጠገን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

በቻይና ሲካሄድ በቆየው ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ላይ የተካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጣሊያኑ አቻቸው ጁሴፔ ኮንቴ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው ወቅትም ጣሊያን የአክሱም ሐውልቶችን ለመጠገንና ጥበቃ ለማድረግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች።

ከዚህ ባለፈም ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ለገበታ ሸገር 5 ሚሊየን ዩሮ እንደሚሰጡም ቃል ገብተዋል ነው የተባለው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉባኤው ጎን ለጎን የተለያዩ የሁለትዮሽ ውይይቶችን በማካሄድ ስምምነቶችን አድርገዋል።

በዚህም ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን በቆይታቸው ፈጽመዋል።

ከቻይናው ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት ውይይትም የሁለቱን ሃገራት ግንኙነት ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ተስማምተዋል።

በተጨማሪም የቻይና እና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎም በርካታ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ለመሰማራት ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የኢሊባባ መስራችና ባለቤት የሆኑት ቢሊየነሩ ጃክ ማ በቀጣዩ ህዳር ወር ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡም አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈም ከተለያዩ ሃገራት ጋር በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ግንኙነቶችን ማጠናከር የሚያስችል ስኬታማ ውይይትም አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ ጉባኤ ቆይታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ገብተዋል።

(ምንጭ፡-ኤፍ.ቢ.ሲ)