በ4ዐ ሚሊየን ዩሮ የሚገነባው የልብ ህክምና ማዕከል የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ

4ዐ ሚሊየን ዩሮ የሚፈጅ አዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ስፔቫላይዝድ ሆስፒታል ተቀመጠ፡፡

በዛሬው ዕለት የተቀመጠው የልብ ህክምና ማዕከል ከሁለት አመት በኋላ ተጠናቆ ለአገልግሎት ይበቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማዕከሉ በኢትዮጵያ መንግስትና በኔዘርላንድ መንግስት የእኩል በእኩል ትብብር የሚሰራ መሆኑን በስነ ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል፡፡

መሰል ዓይነት ማዕከላት እውን መሆን ለጤና ሜዲካል ቱሪዝም አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር የጐላ ድርሻ እንደሚያበረክት የኘሮጀክቱ አስተባባሪና የልብ ህክምና ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ነጋ ገልጸዋል፡፡

የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን ፕሮጀክቱ በሀገሪቱ ከፍተኛ የጤና ቀውስ የሆኑትን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ለመከላከል የሚያስችሉ ኘሮጀክቶችን ለማከናወን ከተያዙት እቅዶች መካከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ለካንሰር የጨረር ህክምና እና ለኩላሊት ንቅለተከላ እንዲሁም ተያያዥ ህክምናዎች የሚያገለግሉ ኘሮጀክቶች በጥቁር አንበሳ ግቢ ውስጥ እውን እንዲሆኑ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ቤንግት ቫን በበኩላቸው መንግስታቸው በእንደዚህ አይነትና ሌሎች ፕሮጀክቶችም ከኢትዮጵያውያን ጋር ተባብረው ለመስራት በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

(ምንጭ፡- የጤና ሚኒስቴር)