በዳንጉር ወረዳ በተፈጠረው ግጭት የ17 ሰዎች ሀይወት አልፏል

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ ዳንጉር ወረዳ፣ አይሻ ቀበሌ በግለሰቦች አለመግባባት በተፈጠረውን ግጭት የ17 ሰዎች ህይወት ማለፉን የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዳይሬክተር አቶ አሰማከኝ አስረስ እንደተናገሩት፣ ግጭቱ የተፈጠረው በዳንጉር ወረዳ አይሻ ቀበሌ በጫኝና አውራጅ ግለሰቦች አለመግባባት መነሻ ሲሆን፣ በተፈጠረው ግጭት የሰው ህይወትና የንብረት ውድመት አጋጥሟል።

በአሁኑ ወቅት ችግሩን ለመፍታት ከአማራና ከቤኒሻንጉል ክልል የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች ወደ ስፍራው በማቅናት የማረጋጋት ስራ እያከናወኑ መሆኑን አቶ አሰማኸኝ ጠቁመው፣ ችግሩ ተባብሶ እንዳይቀጥልና መፈናቀል እንዳይኖር የሁለቱ ክልሎች አመራሮች በስፍራው ተገኝተው በመገምገም ዘላቂ መፍትሄ ያስቀምጣሉ ብለዋል አቶ አሰማከኝ። ይሀንንም ለማድረግ የሁለቱ ክልል መንግስታት ጥሩ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሀድጉ አምሳያ በበኩላቸው፣ የቤኒሻንጉል ክልል ከፍተኛ አመራሮች በአሁኑ ወቅት ችግሩ በተከሰተበት ስፍራ ተገኝተው ከህዝብ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ተከስቶ የነበረው ችግር ከትላንት ምሽት ጀምሮ የቆመ መሆኑንና እስካሁንም ችግሩን አድርሰዋል በሚል የተጠረጠሩ 15 ግለሰቦች መያዛቸውን ገልጸው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሁለቱ ክልል አመራሮች በጋራ ይሰራሉ ብለዋል።