ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ጎበኙ

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ መሀመድ ኡመር ከሱማሌ ክልል የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን ጎብኝተዋል፡፡

ለኦሮሞና ሱማሌ የህዝብ ለህዝብ መድረክ አዳማ የነበሩት ምክትል ርዕሰ-መስተዳድሩ ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለው በአዳማ አካባቢ የሚገኙ ዜጎችን ጎብኝተዋል፡፡

አቶ ሙስጠፋ በጉብኝቱ ወቅት ከሱማሌ ክልል ተፈናቅለው በአዳማ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አካባቢዎችም የሚገኙትን ወገኖች ለማቋቋም መንግስታቸው ጥረት ያደርጋል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ወደቀያቸው ሲመለሱም እንዲቋቋሙ የሚያስችላቸውን ድጋፍ መንግስት እንደሚያደርግም አቶ ሙስጠፋ ተናግረዋል፡፡

የኦዲፒማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በበኩላቸው በአጠቃላይ በአገሪቱ ምንም ዓይነት መፈናቀል እንዳይኖር ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል በጉጂ እና በጌዴኦ አካባቢ ተከስቶ በነበረው ግጭት ተፈናቅለው የነበሩ ወገኖችን ወደቀያቸው መመለስ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ የሱማሌ ተወላጆችንም ወደቀያቸው በመመለስ ለማቋቋም እንሰራለን ብለዋል፡፡

(ምንጭ፡-ኢቲቪ)