በኢትዮጵያ ከ2.5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ መፈናቀሉ ተረጋገጠ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቋቋመዉ የሱፐርቪዥን ቡድን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት 2 ነጥብ 53 ሚሊየን በላይ የሚጠጋ ሕዝብ ከቀየዉ መፈናቀሉን በ አራት ክልሎች በመንቀሳቀስ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ምልከታዉ ያካተተዉ ትግራይን፣ ደቡብ ሕዝቦችን፣ ኦሮሚያን እና አማራ ክልሎችን መሆኑን ቡድኑ ገልጿል፡፡  

በዚህም መሰረት በትግራይ 111 ሺህ 465፣ በደቡብ 873 ሺህ 222፣ በኦሮምያ 1 ሚሊየን 477 ሺህ 720 እንዲሁም በአማራ 107 ሺህ 097 ህዝብ ተፈናቅሏል ብሏል፡፡

የተፈናቃዮችን የትምህርት አገልግሎትና የአልሚ ምግቦች እጥረት ያስተዋለዉ ቡድኑ ተፈናቃዮቹ  ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ ወደቀያቸዉ እንዲመሱ መንግስት መስራት እንዳለበት ቡድኑ አሳስቧል፡፡

እስካሁን በተደረገው ጥረትም ከተፈናቀሉት ዉስጥ 760 ሺህ 000 ያህሉ ወደ ቀያቸዉ መመለሳቸዉን የሰላም ሚንስቴሯ ሙፈሪያት ካሚል ይፋ አድርገዋል፡፡

የምልከታ ቡድኑ አስተባባሪ የሆኑት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸዉ የቡድኑ ሪፖርት ተአማኒ መሆኑን ገልፀዉ መንግስት በሀገሪቱ ያለዉን መፈናቀል እንዲቆምና ተፈናቃዮችም ዘላቂ ኑሮ እንዲኖሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡