በኢትዮጵያ ከ2 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለአደጋ በሚያጋልጡ የስራ ዘርፎች ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

በኢትዮጵያ ከ2 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለአደጋ በሚያጋልጡ የስራ ዘርፎች እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ኢንዳስትሪ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ገለፀ፡፡  

በስራ ላይ በሚገጥሙ አደጋዎች በሃገር አቀፍ ደረጃ ምን ያክል ሰዎች እንደሚጎዱ በውል ባይጠናም በየዓመቱ ግን የስራ ላይ አደጋዎች እየጨመሩ መምጣታቸውን ዓለም አቀፍ የሙያ ደህንነት እና ጤንነት ቀን ሲከበር ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንዳስትሪ አሰሪዎች ኮንፌደሬሽን ዋና ጸሃፊ አቶ ዳዊት ሞገስ እንዳሉት በኢትዮጵያ ከ2 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች ለአደጋ አጋላጭ በሆኑ የስራ ዘርፎች ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

የትምህርት ደረጃቸውም ዝቅተኛ መሆኑ ችግሩን ያጎላዋል ብለዋል፡፡

በስራ ላይ ባሉ ሰራተኞች እየደረሰ ያለው ጉዳት እየጨመረ መጥቷል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌደሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ አያሌው አህመድ ናቸው፡፡

በግንባታ ላይ በየዓመቱ በርካቶች ለህልፈተ ህይወት እየተዳረጉ ነው ያሉት አቶ አያሌው ችግሩን ለመቀነስ ህጎች እንዲወጡና እንዲሻሻሉ ተግባራዊም እንዲሆኑ መደረግ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ዓመት በተደረገ አለም አቀፍ ጥናት 374 ሚሊዮን ዜጎች በስራ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን 2 ነጥብ 78 ሚሊዮኑ ደግሞ ህይወታቸው አልፏል፡፡