ብፁዕ አቡነ ገሪማ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለረጅም ዓመታት በውጭ ግንኙነት የበላይ ሃላፊ በመሆን ያገለገሉት ብጹዕ አቡነ ገሪማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል ።
በሦስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በሰሜን ሱዳን – ካርቱም ኤጲስ ቆጶስነት የተሾሙት ብፁዕ ዶር አቡነ ገሪማ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት፣ ወደ ኋላም የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ብፁእ አቡነ ገሪማ በተለያዩ ሃላፊነቶች ያገለገሉ ሲሆን ከነዚህም መካከል የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጆች ዲን፣ በመንበረ ፓትርያርኩ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ቢሮ ዋና ጸሐፊ፣ የምስካየ ኅዙናን መድኀኔዓለም ገዳም ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ፣ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት የውጭ ግንኙነት የበላይ ኃላፊ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም በሓላፊነትና በአገልግሎት ከሠሩባቸው መካከል፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ምክትል አስተዳዳሪና ዋና ጸሐፊ፣ የትምህርት እና ማሠልጠኛ መምሪያ ሓላፊና ፣ በብሥራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ በመምህርነት አገልግለዋል።
ሥርዐተ ቀብራቸው በመጪው ረቡዕ፣ ሚያዝያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ ከቀኑ 5፡00 በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንዲፈጸም ቋሚ ሲኖዶሱ  መወሰኑ ተጠቁሟል፡፡