ኮርፖሬሽኑ የሚያስገነባቸው ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ገለጸ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚያስገነባቸው ቤቶች በታቀደላቸው የሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቁ ገለጸ፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚና አቶ ረሻድ ከማል ለዋልታ ቴሌቪዥን እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ የመጀመሪያውን ዙር የቤቶች ግንባታ እያከናወነ ሲሆን፣ በሁለተኛ ዙር ለሚስገነባቸው ቤቶች በቅርቡ ጨረታ ያወጣል ብለዋል፡፡

በመጀመሪያው ዙር ባለ 10 ፎቅ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከ20 ፎቅ በላይ የሆኑ ለንግድና መኖሪያ አገለግሎት የሚውሉ ቤቶችን እንደሚገነቡ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው በሁለቱ ዙሮች ለሚገነቡት ቤቶች 7 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ቤቶቹ የሚገነቡት ከዚህ ቀደም የኮርፖሬሽኑ ይዞታ በነበሩ ቦታዎች ላይ መሆኑንም አቶ ረሻድ ጠቁመዋል፡፡

እስከ 4ኛው ፎቅ ድረስ ያለው የህንጻው ክፍሎች ለንግድ እና መሰል አገልግሎቶች የሚውሉ ሲሆን የተቀሩት ለመኖሪያ ይውላሉም ተብሏል፡፡   

ህንጻዎቹ ደረጃቸውን የጠበቁ በመሆናቸው አዲስ አበባን ጽዱና ለኑሮ ምቹ ከማድረግ አኳያ የራሳቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱም ተገልጿል፡፡