4ኛው አገር አቀፍ የጤና ጉባኤ እየተካሄደ ነው

የተለያዩ የምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት 4ኛው አገር አቀፍ የጤና ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

ጉባኤው ከሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፣ በማህበረሰብ ጤና ላይ የተከናወኑ 200 የምርምር ጽሁፎች እንደሚቀርቡበት ይጠበቃል፡፡

የምርምር ግኝቶቹ ለጤናው ዘርፍ የትራንፎርሜሽን እቅዶችን ለማስፈጸም ግብዓት እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡

ለ3 ቀናት የሚቆየው ይህ ጉባኤ በዋናነት በባህላዊ መድሃኒቶች፣ የላባራቶሪ የአገልገሎት ጥራት፣ የስነ ምግብ ጥራት፣ የጤና መረጃዎችና ተላላፊ በሆኑና ባልሆኑ በሽታዎች ኢንዲሁም በመረጃ አጠቃቀም ላይ በዋናነት ትኩረት ያደርጋል ነው የተባለው፡፡

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ ጉባኤው በህብረተሰቡ ላይ የሚታዩ የጤና ችግሮችን ለመፍታት እንዲሁም የተለያዩ የሳይንሳዊ ምርምር ውጤቶች የሚቀርቡበት በመሆኑ ሰፊ ግብዓት ይገኝበታል ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል ሳይንሳዊ ምርምሮችን በጤናው ዘርፍ ላይ ለማካሄድ እንደምገባም ተጠቁሟል፡፡

በጉባዔው በህብረተሰቡ ጤና ላይ ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ የታመነባቸው የምርምር ውጤቶች ለፖሊሲ አውጪዎች እንዲቀርቡና ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ይደረጋል ተብሏል፡፡

በመድረኩም ከ5መቶ በላይ የሚሆኑ የፖሊሲ አውጪ አካላት፣ የፌዴራልና የክልል ጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ በጤና ላይ አተኩሮ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የተለያዩ አካላት ተሳትፈዋል፡፡