ሰብዓዊነት፣ ልማትና ሰላም ተነጣጥለው የሚታዩ አይደሉም – ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ

በዓለም አቀፍ የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን አከባበር ላይ የተገኙት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የበላይ ጠባቂ ሣህለወርቅ ዘውዴ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ሰብዓዊነት፣ ልማትና ሰላም ተነጣጥለው የሚታዩ ጉዳዮች አይደሉም ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ለአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን ፕሬዝዳንቷ በንግግራቸው ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት የኢኮኖሚ መቀዛቀዝን ተከትሎ ድጋፍ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እጃቸው እያጠረ በመሆኑ ማህበሩ ራሱን ለመደገፍ የአገር ውስጥ ገቢ የማሰባሰብ ስራ መስራት እንዳለበትም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ አሳስበዋል፡፡

በጣልያን ወረራ ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመታደግ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ባለፉት 83 ዓመታት ሰብዓዊ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ማህበሩ የቀይ መስቀል አምቡላንስ አገልግሎትን ዘመናዊና ተደራሽ በማድረግ፣ በእሳት፣ በግጭትና በተለያዩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ አደጋዎች የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመከላከል የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

አንደኛው የዓለም ጦርነት ማብቃቱን ተከትሎ እ.ኤ.አ. በ1919 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ በ5 ሀገራት የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማህበር 100 አመት ሊሞላው እንደሆነ ተነግሯል፡፡

ማህበሩ ባለፉት ዓመታት ከፖለቲካና ከርዕዮተ ዓለም ጎራ ወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ሰብዓዊ ተግባራትን ሲያከነውን ቆይቷልም ተብሏል፡፡

የቀይ መስቀልና የቀይ ጨረቃ ቀን በአገራችን “ሰብዓዊነት ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ለ61ኛ ጊዜ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ “ፍቅር” በሚል መሪ ቃል ለ72ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡ (ኢቲቪ)